መስጠት - ወ/ሮ ገነት ዋቅቶላ (የመስጠት በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ) - ሐዋዝ ሀሳብ - Hawaz Hasab
ฝัง
- เผยแพร่เมื่อ 26 พ.ย. 2024
- ይህች ብርቱ ሴት ገነት ዋቅቶላ ትሰኛለች። የ "መስጠት በጎ አድራጎት ድርጅት" መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ናት። ከግል ሕይወቷ ውጣ ውረዶች በአያሌው የተማርኩባት እንስት ናት። ድርጅቷን ፀንሳ ፣ ወልዳና እየተንገዳገደም ቢሆን በእግሩ እንዲቆም የሔደችበትን ትዕግስትም ሳላደንቅ አላልፍም። እልህ አስጨራሽና ተስፋ አስቆራጭ ፈተናዎቿን ታግላ የረታችበትም ፅናት እኔን በብዙ አስተምሮኛል። ገኒ ሲበዛ ትሁት ቅንና ሁሉ ነገሯን ለችግረኞች የሰጠች ደግ ሴት ናት። ያልተነበበች ጥሩ መፅሐፍ ብዬ ብገልፃት እወዳለሁ። ያወኳት ስቀርባት በመሆኑ። ያልገለጡትን መፅሐፍ መች ያነቡታል። ስላላነበቡትስ መፅሐፍ እንዴት ሊናገሩ ይቻላል!
ስራዋን ስትሰራ አትጮህም። ፈጣሪ የፈቀደለት ሰው ድርጅቴን ይጎብኝ የሚል ቀና እምነት አላት። "አቡነ እጨጌ" ባለውለታዋ ናቸው። በሔደችበት ሁሉ ይቀድሙላታል። ከችግሮቿ በፊት ስለምታስቀድማቸው ችግሮቿን ሁሉ ቀርፈው መንገዶቿንም ጠርገው ይጠብቋታል። ቢሮዋ ጠረጴዛ ላይ ስዕለ አድኗቸው ተቀምጣል። የድርጅቴ የበላይ ጠባቂ ናቸው ስትል አንጀት ትበላለች። እምነት እዚህ ድረስ ሲጓዝ ደስ ይላል። ንግግሯ በኩራትና በፈገግታ ይታጀባል። ምንም የሌላት ግን ደግሞ ዕድለኛ ፍጡር ናት። ቢቸግራትም ችግሯ አሸንፏት አያውቅም። ብትንገዳገድም የወደቀችበት ጊዜ የለም። በእርግጥ ወድቃለች ለማለት የፈለኩት ከብዙ ውድቀቶቿ ብዙ ጊዜ እየተነሳች ነው የቆመችው ለማለት ነው። ውድቀት ወድቆ መቅረት እንጂ ወድቆ መነሳት አይደለም። በጎነትን ተደግፎ ማን ይወድቃል። እምነቱን አምኖ ማን ያፍራል። ብቻ ገኒ አልታየችም እንጂ ብዙ የሚታዩ ነገሮች አሏት። አልተሰማችም እንጂ ብዙ ሳቢና ማራኪ ታሪኮች ተሸክማለች። እንደ ፀሀፊ ይህንን ባልፅፍና ባልመሰክር ክስረትም ውድቀትም እንደሆነ አምኜ ነው የማስነብባችሁ። ምንአልባት እሷ ይህን አትሻው ይሆናል። መንፈሳዊ ናትና። ከንቱ ውዳሴ እንዳይሆንባት።
በድርጅቷ ተሳስቼ ይሆናል በቁጥር ከ 20 እስከ 30 የሚደርሱ እናትና ሴት እህቶች እንዲሁም በርከት ያሉ ሕፃናት ታቅፈው ይደገፋሉ። ለሰው ልጅ ትልቁ ስጦታ ገንዘብ አይደለም ብላ ታምናለች። በማዕከሏ ለታቀፉ ወገኖች ተከታታይ የሙያ ስልጠናዎችን ትሰጣለች። እዛው ጊቢያቸው ውስጥ ባለቻቸው አወጥውጠው ይመገባሉ። በግል ህይወታቸው ዙሪያም እንደ እህትና እንደ ልጅ ሆና በመቅረብ ታማክራቸዋለች። ለደካሞቹ ቀለብ ትሸምታለች። ልጆቻቸውን በማዕከሉ ማቆያ በማሳረፍ ትንከባከባለች። ሌላም ሌላም። ሰልጥነው ለሚወጡት ስራ መጀመሪያ ቁሳቁሶችንና ጥቂት ጥሪት ትሰጣለች። ለውጣቸውን ሳትታክት ትከታተላለች። ብቻ አቀራረቧ ሁሉ ውብ ነው። መልካም እናትነትን ይመስላል። ለሁሉም ቅርብና ነፃ የሆነች ናት።
ሌላው ደስ ያለኝ ነገር በማዕከሉ ያሉ እናቶችና እህቶች በፈትል ፣ በጥልፍ ፣ በስፌት ፣ በፀጉር ስራ ፣ በሽመናና በሌሎችም የሀገራችን ድንቅ ባህላዊ ጥበቦች ዙሪያ በወጉ ይሰለጥናሉ። ሰልጥነው ያመርታሉ። አምርተውም ይሸጣሉ። ድንቅ መስጠት ይሏችኋል ይህ ነው! ለሰው ልጅ የማያልቀውን ጥበብ መስጠት። በጥበቡም እየተጠበበ እንዲኖር መፍቀድ። ከተረጂነት እንዲላቀቅ መንገዱን ማሳየት። እኔ ልሒድልህ አለማለት። እኔ ላኝክና ላላምጥልህ ብሎ አለመሳሳት እንዴት ያስደስታል። ሰው በተፈጥሮው የላቡን ውጤት መብላት ያረካዋል። ቸግሮትና ጨንቆት ካልሆነ በቀር ተመፅዋችነትን የሚሻ ያለ ሰው አይመስለኝም። አንዳንድ ባይጠፉም። የሆነው ሆኖ ገኒ በብዙ ነገሮች ልትታገዝ ብትችል ብዙ ወገኖችን በብዙ አቅጣጫ ልትቀይር የምትችል ታታሪ እህት ናት።
እኔ ሳውቃት አቅሟ እጅግ ውስን ነው። እናም እስኪ ጊዜአችሁን እያመቻቻችሁ ከወዳጅ ዘመዶቻችሁጋ በመሆን ትንሽ ድጋፍን ሸክፈችሁ ጎብኟት። በድርጅትና በቡድን ሆናችሁ ወደማዕከሏ በመሔድም ምን ጎደለሽ በሏትና ክፍተቷን ሙሉላት። ዕውቀታችሁንም ፈሰስ አድርጉና እናትና እህቶቻችንን በሙያም በስነ - ልቦናም አሰልጥኑ። አቅማችሁ በፈቀደም መጠነኛ የገንዘብ እርሾን በድርጅቷ አካውንት ጠብ እያደረጋችሁ ጥረቷን አበርረታቱ። እናም እኔ እንዲህ እላችኋለሁ። "አንድ ሰው አስቦ አንድ በሬ ስቦ አይሆንም" በመሆኑም ሰንሰለት በሰራ ትብብር አጠገቧ እንሁንና የደግነት ከፍታዋ ይበልጡን የተዋጣለት እንዲሆን እጆቻችንን እናጋራት። ብዙ ነገር ማለት ብችልም በዚሁ ላብቃ።
አድራሻ ፦
ኮተቤ መሳለሚያ (ሳራ መናፈሻ አጠገብ)
ባንክ አካውንት ቁጥር፦
Mestet Charity Organization
1. Commercial Bank Of Ethiopia
1000472532085
Mestet Charity Organization
2. Awash International Bank
01308613750600
ሞባይል ቁጥር፦
+251922529997
+251945222224
"ሐዋዝ" የግዕዝ ቃል ሲሆን ፤ ትርጓሜውም "የሚያምር" ፣ "ደስ የሚል" ፣ "መልካም" እና "ቆንጆ" የሚል ነው፡፡ ይህንን ውብ ኢትዮጵያዊ ቃል የ "ዩቲዩብ ቻናላችን" መጠሪያ ስም አድርገን የተጠቀምንበት ዋና ምክንያት ፤ በዩቲዩብ ቻናላችን ላይ የሚለቀቁ ሀሳቦች ሁሉ ፤ ከመዝናኛነት በዘለለ … ደስ የሚሉ ፣ የሚያምሩ ፣ እንዲሁም የሰው ልጆችን አዕምሮ ፤ በበጎ ሊያንፁ የሚችሉ ፤ ቅንና ጠቃሚ ጭብጦች የሚተላለፉበት ቻናል እንደሚሆን ፍፁም በመተማመን ነው፡፡